Fana: At a Speed of Life!

አቶ መላኩ አለበል ከአለም ባንክ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከአለም ባንክ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ፡፡
ውይይቱም የኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ሂደት ላይ ያተኮረ መሆኑ ታውቋል፡፡
በውይይቱ የአለም ባንክ ልዑክ መሪና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ኦስማን ዲዮን ኢትዮጵያ ምርትን ለውጭ ሀገራት ገበያ ከማቅረብ ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ለፈጣራ ምቹ አካባቢን ከመፍጠር እና በንግድ ግንኙነት ዙሪያ ከእስያ ሃገራት በተለይም ከቬትናም መማር አለባት ብለዋል፡፡
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው÷ ከአለም ባንክ ልዑክ ጋር እንዲህ ያለ ውይይት በመደረጉ እና የአለም ባንክ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
እንዲሁም በሃገሪቱ ያለውን ስራ አጥነት ፣ ድህንነት እና የዋጋ ግሽፈት በማንሳት የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ለመቅረፍ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሌሎች የልማት ስራዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ፣ የንግድ ሥራን ለማመቻቸት እና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመንደፍ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም በሀገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ልማት የተመዘገበ መሆኑ አንስተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ተፅእኖን በተመለከተም የግብርናው ዘርፍ ባይጎዳም በአገልግሎት እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከንግድና ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዝግጅት ጋር በተያያዘ የውጭ ምንዛሪ ችግሮችን ለመፍታት ከአለም ባንክ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ለዚህም ተስፈኛ መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ ከልዑካኑ ጥሩ ምልክት ማየታቸውን መናገራቸውን ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.