ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ተቀናጅቶ መሥራት ይገባል – ዶክተር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነትና በዘላቂነት ለማቋቋም የተቀናጀ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሯ በአፋር ክልል ከአሚባራ እና ሀሮካ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከፈንታሌ ወረዳዎች በአዋሽ ወንዝ ሙላት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ መመልከታቸው ተነግሯል፡፡
ዶክተር ሊያ በጉብኝቱ ወቅት የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው በመስራት ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሄ መሻት ይገባቸዋል ሲሉ ነው ያነሱት፡፡
የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከባድ ቢሆንም የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በጊዜያዊ መጠለያ ማስፈር መቻሉ የሚደነቅ ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በቀጣይም እንደወባ፣ ኮሌራ እና ሌሎች መሰል ወረርሽኝ በሽታዎች ችግር እንዳይፈጥሩ የጤና ሚኒስቴር ከክልል ጤና ቢሮዎች ጀምሮ እስከ ቀበሌ ካሉ የጤና ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ የተፈናቃይ ተወካዮች በበኩላቸው ሚኒስትሯ ያለባቸውን ችግር በአካል ለማየትና ለመረዳት በስፍራው በመገኘታቸው ማመስገናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በተለይ ከህክምና ጣቢያዎች መውደም፣ ከአምቡላንስ፣ ከህክምናና መድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለተከሰቱ ችግሮች ጤና ሚኒስቴር አስቸኳይ እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትሯም በዕለቱ በሁለቱም ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የመድሃኒትና የህክምና ግብአቶች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሄ ለማግኘት እንጥራለን ብለዋል፡፡
በተቻላቸው መጠን በችግራቸውም ውስጥ ሆነው ኮሮናን እንዲከላከሉ አደራ ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡