Fana: At a Speed of Life!

በመስቀል ደመራ በዓል የታየው የአብሮነት እና ሰላማዊ የበዓል አከባበር በኢሬቻ በዓልም ሊደገም ይገባል – ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመስቀል ደመራ በዓል የታየው የአብሮነት እና ሰላማዊ የበዓል አከባበር በኢሬቻ በዓልም ሊደገም እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
 
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም በመጠናቀቁ እና የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ ክብረ በዓል አከባበር ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
 
ምክትል ከንቲባ አዳነች የመስቀል ደመራ በአል በሰላም እንዲከበር አስተዋጽኦ ላደረጉ የሀይማኖት አባቶች ፣ምእመናን እና ፀጥታ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
 
የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ባስቀመጠው የሰው ቁጥር መሰረት የሚከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ ክብረ በዓል በመስቀል ደመራ በአል ዕለት በታየው የአብሮነት እና የትብብር መንፈስ በሰላማዊ መንገድ መከበር ይኖርበታል ብለዋል።
 
ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የሰላም ፣ የእርቅ እና የመሰባሰብ በዓል መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ የበዓሉ ተሳታፊዎችም ከአባ ገዳዎች የተላላለፈውን መልዕክት በመገንዘብ እንዲያከብሩ ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
የኢሬቻ በዓል የሰላም እና የአብሮነት በዓል ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች ክብረ በዓሉን ለሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያነት ለማዋል ከሚጥሩ አካላት በመጠበቅ በዓሉ በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበዓሉ ተሳታፊ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በዓሉን ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ለማክበር የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ተሰናድተዋል ተብሏል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.