የአማራ ልማት ማኅበር 1 ሺህ 255 የመማሪያ ሕንጻ ለመገንባት ማቀዱን ገለጸ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በ2013 ዓ.ም 5 ሺህ 20 መማሪያ ክፍሎች የሚኖራቸው 1 ሺህ 255 አዲስ ሕንጻዎችን ለመገንባት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
ይህም በ2012 ዓ.ም ተገንብተው ከተጠናቀቁት እና በተለያዩ የግንባታ ደረጃ ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ የሚሠራ ነው ተብሏል።
ማኅበሩ በትምህርቱ ዘርፍ በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁሞ ÷ የተጀመሩ የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ለማጠናቀቅ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር፣ ለቴክኒክና ሙያ ፕሮጀክቶች እና ለጤናው ዘርፍ ልማት 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ዓመታዊ በጀት መመደቡንም አስታውቋል።
ከዚህ ውስጥ ወደ 2 ቢሊየን ብር ገደማ የሚሆነውን ለአዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ወጪ እንደሚያደርግ የማኅበሩ የፕሮጀክት ትግበራና ክትትል ዳይሬክተር የኔውጓድ እስቲበል ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቤቶች የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ እና የተማሪ እና የመማሪያ ክፍል ጥምርታውም ከደረጃ በታች መሆኑ ይነገራል።
አልማ በሦስት ዓመታት ውስጥ የጥራት ደረጃ ያሟሉ ትምህርት ቤቶችን ከ16 በመቶ ወደ 50 በመቶ ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ እቅድ አውጥቶ እየሠራ ይገኛል ተብሏል።
ለዚህም የነባር ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እና ምንም በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል።
ህብረተሰቡም የችግሩን መጠን በመረዳት የራሱን ችግር በራሱ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ መቅረቡን አብመድ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።