Fana: At a Speed of Life!

ትራምፕና ባይደን የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያውን የገፅ ለገፅ ክርክር ሊያካሂዱ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና እጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያውን የገፅ ለገፅ ክርክራቸውን ሊያካሂዱ ነው፡፡

ትራምፕና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ባይደን ሌሊት ከሚያካሂዱት የገፅ ለገፅ ክርክር በተጨማሪ ሁለት ክርክሮች ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

ክርክሩን የፎክስ ኒውሱ አዘጋጅ ክሪስ ዋላስ እንደሚመራው ተሰምቷል፡፡

ኮሮና ቫይረስ የተመረመሩ 70 ሰዎች ክርክሩን እንደሚታደሙም ተነግሯል፡፡

የፕሬዚዳንታዊ ክርክሩ ኮሚሽን ሌሊት የሚካሄደው ክርክር ትራምፕና ባይደን ባስመዘገቧቸው ውጤቶች፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳይ፣ በኮቪድ 19፣ በኢኮኖሚ፣ የዘር እና በከተሞች ውስጥ በሚታየው ግጭትና በምርጫው ተዓማኒነት ዙሪያ ያተኩራል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ሰሞኑን ኒውዮርክ ታይምስ ዶናልድ ትራምፕ ላለፉት 10 ዓመታት የገቢ ግብር አልከፈሉም ሲል መዘገቡ ይታወቃል፡፡

ይህም ኮቪድ 19 ካሳደረው ተጽዕኖ በተጨማሪ ጆ ባይደን ተቀናቀኛቸውን የሚረቱበት ጠንካራ ጭብጥ እንደሚሆናቸው እተነገረ ይገኛል፡፡

ባይደን ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ያነሳሳቸው በቨርጂኒያ የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች ያደረጉትን ሰልፍ ተከትሎ ትራምፕ ባለማውገዛቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡

በዚህም ጆ ባይደን ትራምፕን አገሪቱ የቆመችበትን መሰረት የሚሸረሽር ድርጊት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡

ትራፕም በበኩላቸው የ77 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ባይደን እርጅና ተጭኗቸዋል አገሪቷን ለመምራትም ብቁ አይደሉም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በተጨማሪም 34 ቀናት በቀሩት በዚህ ምርጫ ባይደን ከተመረጡ አሜሪካንን ወደ ባሰ ቀውስ እንደሚዘፍቋት ተናግረዋል፡፡

በጥቅሉ ዛሬ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ክርክር የኮሮና ቫይረስ ቀውስ መድረኩን ይቆጣጠረዋል ተብሎ ተጠብቋል፡፡

 

ምንጭ፡-ሲኤንኤን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.