Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ለሰላም ለተጉ አምባሳደሮች ክልል አቀፍ የእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርአት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል ለሰላም ለተጉ አምባሳደሮች ክልል አቀፍ የእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርአት በሀዋሳ ከተማ ተካሄደ፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሀገራችንን ህዝቦች የአብሮነትና የመተጋገዝ እሴቶችን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት አመታት የሀገሪቱን አንድነትና የህዝቦችን አብሮነት ለአደጋ ያጋለጡ ችግሮች ማጋጠማቸውን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በተለይ የተሳሳቱ ትርክቶች የፈጠሯቸው ችግሮች ግጭትና የሰላም መደፍረስ ሁኔታዎች የህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መፍጠራቸውን አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት የህዝቦች የአብሮነትና የመታጋገዝ እሴቶች ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበር ገልጸዋል።

አሁን መልክ እየያዘ ለመጣው ሰላማዊ ሁኔታ ብዙዎች የተለያየ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ጠቅሰው ለዚህም ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በተለይም አሁን ለሚታየው ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባቶች እንዲሁም የጸጥታ ሃይሎች እውቅናና ምስጋና ቢያንሳቸው እንጅ አይበዛባቸውም ሲሉም ነው የተናገሩት።

ይህን ሰላምና መረጋጋት የህዝቡን የቆየ የወንድማማችነት፣ የመተሳሰብ፣ የፍቅርና የአንድነት እሴቶች ማጠናከር እንደሚገባም አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአብሮነት ተምሳሌት የሆነው የደቡብ ክልል መንግስትና ህዝብ ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ማድረጉን ጠቁመው ጊዜያዊ ፈተናዎችን በመመከትና በመተባበር የሀገሪቱን አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ አውስተዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የሰላምን ዋጋ በሚገባ በመረዳት ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል ነው ያሉት።

የኦሮሚያና ሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ከደቡብ ክልል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ለሰላም መስፈን በጋራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

እውቅና የተሰጣቸው ባለፉት ሁለት አመታት በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ከአካል ጉዳት እስከ መስዋዕትነት ለከፈሉ የጸጥታ አካላትና የሰላም አምባሳደሮች ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በልዩ ሁኔታ ለክልሉ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ መከላከያን ጨምሮ የክልሉ የጸጥታ አካላት እና የሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች የእውቅናና የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

መረጃው የደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.