በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡
ክሱ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገ መንግስት እና ፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክስ የተከፈተ ሲሆን ተከሳሾቹ በተረኛ ችሎት በዳኛ ፅህፈት ቤት ቀርበው ክሱ ደርሷቸዋል፡፡
ከባለሙያ ጋር ተማክረውም ክሱን በባለሙያ ለማሰማት ለመስከረም 26 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ግለሰቦቹ አንደኛ ጥላሁን ያሚ ባልቻ፣ ሁለተኛ ከበደ ገመቹ መገርሳ፣ ሶስተኛ አብዲ አለማሁ በዳኔ እና አራተኛ ላምሮት ከማል መሃመድ ናቸው፡፡
ግለሰቦቹ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆኑ፥ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1 ሺህ 176/2012 አንቀፅ 3/2 የተደነገገውን በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ወንጀል ተከሰዋል፡፡
አቃቤ ህግ ያልታወቀ የኦነግ ሸኔ አባል እንዲሁም አንድ ግለሰብ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም አንደኛ ተከሳሽን ገላን ኮንዶሚኒየም በማግኘት መንግስት ለኦሮሞ ህዝብ አልጠቀመም አንድ ላይ በመስራት ከስልጣን ማስወገድ አለብን፤ ከስልጣን እንዲወገድ ደግሞ የተመረጡ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰድ አለብን፤ የእርምጃ አወሳሰዱን ሂደት ደግሞ እንነግርሃለን በማለት እና እሱም ዝግጁ ሆኖ በመጠበቅ ለሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች ሃሳቡን በማጋራት እና ሲያሴሩ መቆየታቸውን አቃቤ ህግ ጠቅሷል፡፡
በዚህ መሰረት ሁለተኛ ተከሳሽ ቀድሞ ገዝቶ አስቀምጦ የነበረውን ስታር ሽጉጥ ከአምስት ጥይቶች ጋር ለአንደኛ ተከሳሽ አስረክቦ የሚገሉትን ሰው እስኪገድሉ እና ትዕዛዝ እስኪሰጣቸው ሲጠብቁ እንደነበር ተገልጿል፡፡
አራተኛ ተከሳሽም ስሙ ካልታወቀ የኦነግ ሸኔ አባል ጋር ከተፈላጊው መካከል አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ነግሯት አርቲስቱን ስታገኘው ለኦነግ ሸኔ አባል ቀድማ በማሳወቅ ወደ ሚነግሯት እና እርምጃው ወደሚወሰድበት ስፍራ አርቲስቱን እንድታደርስለት የተሰጣትን ተልዕኮ በመቀበል ስትዘጋጅ እንደነበር አቃቤ ህግ ጠቅሷል፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ባቀረበው ክስ እንደሚያመለክታው በሰኔ 22/2012 ዓ.ም ከቀኑ 12 ሰዓት ላይ አርቲስቱ በቀጠሮው በመገኘት አራተኛ ተከሳሽ ግለሰቧን በሚያሽከረክረው መኪና ወደ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ወደ አንዶዴ የባቡር ጣቢያ አቅጣጫ እንዲወስዳት በማድረግ ገመቹ የተባለውን ያልተያዘ ግብረአበራቸው አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተው ካሉበት ቦታ በመጥራት የአርቲስቱ ተሸከርካሪ በቦታው መድረሱን በማመላከት እንዲገደል ትዛዝ በመስጠት አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች ትዕዛዙን በመቀበል መኪናውን በመከተል አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ገላን ኮንዶሚኒየም ወደ እንዶዴ ባቡር ጣቢያ መግቢያ ከምሽቱ 3፡30 ላይ ተሸከርካሪው እንደደረሰ አራተኛ ተከሳሽ ጤንነት አልተሰማኝም መኪናውን መንገድ ዳር ላይ አቁመህ እረፍት ላድርግ በማለት እንደጠየቀችው ጠቅሷል፡፡
አርቲስቱም ተስማምቶ መኪናውን መንገድ ዳር አቁሞ ባለበት አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች በቦታው በመድረስ አንደኛ ተከሳሽ ወደ ሟቹ (ወደ አርቲስቱ) ሲያመራ ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ ሟቹ በጋቢና በኩል ወጥቶ እንዳያመልጥ ሲከታተል፣ሶስተኛ ተከሳሽ ደግሞ በመኪና ጀርባ በመሆን ሰው እንዳያያቸው አካባቢውን ሲቃኝ አንደኛ ተከሳሽ ይዞት የነበረውን ስታር ሽጉጥ በመተኮስ የሟች ግራ ደረትን ከጀርባ መምታቱን አቃቤ ህግ ጠቅሷል በክሱ፡፡
ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ተከሳሾች አካባቢውን ለቀው ሲሄዱ አራተኛ ተከሳሽ ደግሞ በቦታው እንዳለች የተያዘች በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የሽብር ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በታሪክ አዱኛ