የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አባገዳዎች ፣ አደ ስንቄዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተከበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ዕቅድ በማውጣት እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየት ወደ ስራ መግባቱን ኮሚሽኑ አስታውሶ ልዩ ልዩ አካላትን ያሳተፈ የፀጥታ ስራ በመሰራቱ በዓሉን በሰላም ማክበር እንደተቻለም አስታውቋል፡፡
ለበዓሉ ስኬታማነት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት፣ የበዓሉ ታዳሚዎች ላደረጉት ቀና ትብብር ደከመን ሰለቸኝ ሳይሉ ህዝብና መንግስት የጣሉባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለተውጡ ለከተማው አስተዳደር፣ ለሀገር መከላከያ፣ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ለሪፐብሊካን ዘብ ፣ ለፌደራል፣ ለኦሮሚያና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችና አባላት በፀጥታ ግብረ ኃይሉ ስም ኮሚሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
በተለይም መላው የከተማችን ነዋሪዎች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ለማስቻል መረጃዎችን ለፀጥታ ኃይሉ በማቀበል የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይከሰት በፖሊስ የተላለፉ መረጃዎችን በመቀበልና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ተባባሪ በመሆን ህብረተሰቡ ለነበረው የተለመደ ቀና ትብብር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋናውን በማቅረብ በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መልካም ምኞቱን ይገልፃል፡፡