Fana: At a Speed of Life!

ሃገር አቀፍ የትምህርት ብርሃን የተሰኘ አዲስ የፈተና ዓይነት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው አመት “ሃገር አቀፍ የትምህርት ብርሃን” የተሰኘ አዲስ የፈተና አይነት እንደሚጀምር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የትምህርት ዘርፉን የሪፎርም ስራዎች በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ መደበኛ ትምህርትን ሳይከታተል በሌላ አጋጣሚ ማንበብና መጻፍ የቻለ ማንኛውም ግለሰብ ይህን ፈተና በመውሰድ የሶስተኛ ክፍል ማረጋገጫ ሰርትፊኬት ይሰጠዋል ብለዋል።

ሚኒስትሩ አሁን ላይ በሃገሪቱ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ወይም የተማረ ማህበረሰብ 43 በመቶ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ የፈተና መርሃ ግብር በተለያየ መልኩ ማንበብና መጻፍ ችለው በመደበኛ ትምህርት ያልተካተቱትን ማረጋገጫ እንዲያገኙ እንደሚረዳ ጠቁመው የተማረውን የማህበረሰብ ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገውም አስረድተዋል፡፡

ፈተናው በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚሰጥና ፈተናውን ያለፉት በተግባር ተኮር ትምህርት እንዲቀጥሉ ይደረጋልም ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በዘንድሮው አመት የሙያ ትምህርቶችን በተወሰነ መልኩ ለ11ኛ ና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለመስጠት መታቀዱንም አንስተዋል።

ይህም ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የሙያ ባለቤት ሆነው እንዲጨርሱ ያግዛቸዋል ተብሏል።

በሃይማኖት ኢያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.