በትግራይ ክልል የሚገኙ ዐቃቤ ህጎች በክልሉ መንግስት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና ውሳኔ ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል የሚገኙ ዐቃቤ ህጎች በክልሉ መንግስት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና በአመራሮቹ ፓለቲካዊ ጫና ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ ነው።
ባለብን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ምክንያት ሥማችን አይጠቀስብን ያሉ አቀቤ ህጎች እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግሥት የፓለቲካ ጣልቃ ገብነት ስራቸውንም ኑሯቸውንም እየጎዳው ነው።
የፖለቲካ አመራሮች በደል መገለጫው ብዙ ቢሆንም ዋናው ከሙያ ነጻነት ማጣት እና ከደመወዝ ክፍያ ፍትሃዊነት መጓደል ጋር በተያያዘ ያቀረቡትን ተደጋጋሚ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ዐቃቤ ህጎችን ከሥራ ለመቀነስ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ እና ተደጋጋሚ በሆነው የክልሉ መንግስት የፓለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ከነገ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ መሆኑን አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ ዐቃቤ ህጎች ደመወዝ በሌሎች ክልሎች ካሉ ተመሣሣይ ዐቃቤ ህጎች በጣም ያነሰ ነው፤ ይህ እንዲስተካከል ቢጠይቁም የክልሉ መንግስት ቃል ከመግባት ባለፈ ሊያስተካክል እንዳልቻለ መናገራቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
የክልሉ መንግስት ኢፍትሃዊነት ከሌሎች ክልሎች ዐቃቤ ህጎች አንጻር ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል ካሉ ዳኞች ደመወዝም በእጅጉ ያነሰ ነው ብለዋል።
ጥያቄያችን ብዙ ነው ያሉት ዐቃቤ ህጎቹ፤ “ቅድሚያ በክልሉ በተባባሰው የኑሮ ውድነት ምክንያት እየደረሠብን ያለውን ጫና ለመቋቋም ጥያቄያችን ይመለስልን ብለን እንጂ በተቋሙ ላይ ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሥራችንን በነጻነት እንዳንሰራ እያደረገን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ጥያቄያቸውን እንደሚመልስላቸው በመግለጽ አድማውን እንዳይመቱ በመወትወት ላይ እንደሚገኝ የጠቀሡት ዐቃቤ ህጎቹ፤ በደረሳቸው መረጃ መሠረት ደመወዙን ከማስተካከል ይልቅ የዐቃቤ ህጎችን ቁጥር ለመቀነስ እየሠራ ነው ብለዋል።
በሥራቸው ላይ በክልሉ መንግሥት እየተደረገባቸው ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትም ለትግራይ ህዝብ ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት እንዳዳገታቸው ነው የተናገሩት።
ስለሆነም ቀጣዩ ጥያቄያቸው በተቋማቸው ውስጥ ሙያዊ ነጻነት እንዲከበር ማድረግ መሆኑንም አስታውቀዋል።