Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድባጢ ወረዳ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ 213 የህብረተሰብ ክፍሎች ወደቀያቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ድባጢ ወረዳ ቆርቃ እና ሰንቦሰሬ ቀበሌዎች ከዚህ ቀደም የጥፋት ኃይሎች በሚያደርሱት ጥቃት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ 213 የህብረተሰብ ክፍሎች ወደቀያቸው ተመለሱ፡፡

በወረዳው በሚገኙት ቆርቃ እና ሰንቦሰሬ ቀበሌዎች ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የጥፋት ኃይሎች በሚያደርሱት ጉዳት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በጋሌሳ ማዕከል ጊዜያዊ መጠለያ ቆይተዋል፡፡

እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በንጹኃን ዜጎች ላይ ግድያ በመፈጸም፣ መሳሪያ በመንጠቅና በማስፈራራት ህብረተሰቡን ሲያሸብሩ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የክልሉና የፌደራል የጸጥታ አካላት በአካባቢው ያለውን የጸረ-ሠላም እንቅስቃሴ ለመደምሰስ በትኩረት እየሰሩ ይገኛል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም በአካባቢው ተገኝተው ከህብረተሰቡ ጋር ተደጋጋሚ የውይይት መድረኮችን አካሂደዋል፡፡

በዚህም በተለይም ከሁለቱ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ 44 አባወራና እማወራዎች በቁጥር ደግሞ 213 የሚሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ትናንት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡

ወደቀያቸው ከተመለሱት ውስጥ 94 ወንዶች ሲሆኑ 119ኙ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.