የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከግብፁ አቻቸው አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣መስከረም 25 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከግብፁ አቻቸው አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር መወያየታቸው ተገለፀ።
በዚህም በሀገራቱ ቀጠናዊ የሰላም ፣ ደህነነት፣ ንግድ እና የኮሮና ቫይረስ ምላሽ ትብብር ላይ በማተኮር መወያየታቸውን ከኬንያ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ግብጽ ከኬንያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት እና ትብብር በማድነቅ ከሀገሪቱ ጋር ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙት ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።
እንዲሁም ልምድ ያላቸው የግብፅ ኩባንያዎች በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በመሰረት ልማት እና በሌሎች ዘርፎች በኬንያ እንዲሰማሩ ፍላጎታቸው መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በተመሳሳይ ኡሁሩ ኬንያት ሀገራቸው ከግብፅ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያየ ዘርፎች ማጠናከር እንደምትፈልግ አንስተዋል፡፡
አያይዘውም የግብፅ ኩባንያዎች በኬንያ በመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሰማሩ ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በምስራቅ አፍሪካ የሰላምና ደህነት ጉዳይ እንዲሁም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።