የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሃገር አቀፍ የሁኔታ ግምገማና እቅድ ውይይት እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሃገር አቀፍ የሁኔታ ግምገማና እቅድ ውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።
በዋና ፅህፈት ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት መድረኩ ለ2013 ዓ.ም የታቀዱ ዋና ዋና ስራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫ ይዞ በጋራ መረባረብ ማስቻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
አቶ ተስፋዬ እንደ ሃገር ሁሉን አቀፍ የለውጥ ስራ ውስጥ እንገኛለን ማለታቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ይህን ለውጥ እየመራ ባለፈው ግማሽ ምዕተ አመት ሳይመለሱ የቆዩ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ እኩልነትና ዴሞክራሲ በአግባቡ መመለስ የሚያስችል እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጎንለጎን የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ የመመለስ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ ላለመቀበልና ከተቻለ ለመቀልበስ የሚሰሩ ጥቅማቸው የተነካባቸውና ሌሎች ፅንፍ የረገጠ አካሄድ የመታገል ስራዎች ከህዝቡ ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ለእነዚህ ትላልቅ ስራዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ባለው መልኩ የጋራ ትልም ተይዞ የጋራ ርብርብ እንዲደረግ መድረኩ አቅጣጫ ያስቀምጣልም ነው ያሉት።
በመድረኩ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።