Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 25 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በበጀት እጥረት እና በአንዳንድ ችግሮች የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና ከብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ጋር በመሆን የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት ምክትል ከንቲባዋ በከተማዋ በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በማስቀረትና በቂ የመንገድ ሽፋን በመፍጠር ለመኖር ምቹ የሆነች አዲስ አበባን እንገነባለን ብለዋል፡፡

በተለይ የገቢና ወጪ ንግድ ኮሪደር የሆኑ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ በሆኑ አካባቢዎች የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ከበጀት ጀምሮ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

የተደረገው የጋራ ጉብኝትም ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልገው የማስፈጸሚያ በጀት ከተለያዩ አጋር አካላት ለማፈላለግ በማሰብ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው በስራ ተቋራጮች እየተገነቡ ከሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ርዝመታቸው 34 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑ ነው የተናገሩት፡፡

መንገዶቹን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ – በአቃቂ ድልድይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ፣ ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ – ቡልቡላ – ቂሊንጦ አደባባይ ፣ ቡልቡላ ካባ መግቢያ መድኃኒዓለም እና የቦሌ ሚካኤል አደባባይ ላይና ታች – ቡልቡላ ካባ መግቢያ መንገዶችን እንዲሁም የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች ዛሬ ከተጎበኙት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.