በጋምቤላ ክልል አንዳንድ ወረዳዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ከ4 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል አንዳንድ ወረዳዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ከ4 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገለፀ።
በክልሉ ኑዎር ዞን ዋንቱዋ ወረዳ በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከ16 ቀበሌዎች ከ4 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተነግሯል፡፡
በተመሳሳይ በክልሉ በጎርፍ አደጋ ምክንያት በላሬ ወረዳ በ28 ቀበሌዎች የሚኖሩ ቁጥራቸው ያልተገለፀ የህብረተሰብ ክፍሎች መፈናቀላቸው ተጠቁሟል፡፡
በወረዳው በደረሰው የጎርፍ አደጋ በቤት እንስሳትና የተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ ከፍተጋኛ ጉዳት መድረሱን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጋርዊች ቤል ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው ጎርፍ የደረሰበት የኢታንግ ልዩ ወረዳ ሲሆን የዘድሮው ክስተት ከአምናው የባሰ ሲሆን በአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ህብረተሰቡ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ በአፋጣኝ እንደሚያስፈላጋቸው የኢታንግ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡኬሎ ኦቦንግ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በጎርፍ አደጋው ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡
ዘንድሮ የወንዞች መሙላትን ተከትሎ ከአምናው የበለጠ የጎርፍ አደጋው ሊከሰት ስለሚችል የህብረተሰቡን ህይወት ለመታደግ ወደ ደረቃማ አካባቢዎች እዲሰፍሩ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኑዎር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሙድ ቶክ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲም በክልሉ በጎርፉ ምክንያት አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች ከፌደራል መንግስት የተሰጠውን የእህል ድጋፍ ጨምሮ የክልሉ መንግስት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የእህል እና የቁሳቁሰ ግዠ በመፈጸም ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ የውሃ ላይ ትራንሰፖርት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ትራንስፖርት በሚደርሰባቸው አካባቢዎችም ለመጀመርያ ተጎጂዎች ድጋፍ መስጠት መጀመሩን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡