በመዲናዋ በተያዘው አመት 525 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ መንገዶች የጥገና ስራ ይከናወናል- ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመዲናዋ በተያዘው አመት በተለያዩ አካባቢዎች 525 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ መንገዶች ጥገና ስራ ለማከናወን እቅድ መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በ2013 በጀት አመት 525 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት፣ የድልድይ፣ የድሬኔጅ ፣ የአክሰስ መንገድ እና ሌሎች በርካታ ልዩ ልዩ የጥገና ስራዎችን ለማከናወን ማቀዱን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
በዚህም 130 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ጥገና፣ 68 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ጥገና፣ 50 ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን መንገድ ጥገና፣ 20 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንድና ከርቭስቶን ጥገና፣ 257 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር ጥገናና የፉካና ቦይ ጠረጋ ስራዎች እንዲሁም የማንሆል ክዳን ፣የድጋፍ ግንብና የድልድይ ጥገና ስራዎች የሚከናወን ይሆናል፡፡
በተጨማሪም በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች መደበኛና ወቅታዊ ተደራሽ ጥገና ማድረግ፣ በነባር መንገዶች የከርቭስቶን ግንባታ ማከናወን፣ የመንገድ ዳር መብራት ጥገና ስራዎችን ማከናወንና ሌሎች ጥገና የሚያስፈልጋቸው ስራዎችን በራስ ኃይል ለማከናወን እቅድ መያዙ ታውቋል፡፡
የጥገና ስራው የሚከናወነውም በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች የትራፊክ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉሉ ብሎም ለእግረኛ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ መሆኑን ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከጥገና ስራዎቹ ጋር በተያያዘ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2012 በጀት አመት 544 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የጥገና ስራዎችን ማከናወኑን ገልጿል፡፡