የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በኦላይን ለመፈተን የሚያደርገውን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በኦላይን ለመፈተን የሚያስችለውን አስፈልጊ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ለባለሙያዎች ስልጠናዎችን መስጠት የተጀመረ ሲሆን በትምህርት ቤቶችም ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል በቂ የመብራት እና የኔትዎርክ አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኦላይን የሚሠጠው ፈተናም ኩረጃን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ከመሆኑም ባሻገር ለወረቀትና ፈተናውን ለማረም የሚወጣውን ወጪና ጊዜ ይቆጥባል ነው የተባለው፡፡
ቴክኖሎጂው የተለያዩ ሲስተሞች የተጫኑበት ሲሆን ተማሪዎች ፈተናውን በሚወስዱበት ጊዜ የራሳቸው ታብሌት ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስችል ሲስተም አለው ተብሏል።
ፈተናው የሚሰጥባቸው ታብሌቶችም በቅርቡ ለተማሪዎች እንደሚሰራጩ ተገልጿል።
ተማሪዎችም ከቴክኖሎጂው ጋር እንዲተዋወቁ ከሦስት ሣማንት ያላነሰ ጊዜ የሚሰጣቸው ሲሆን ምንም ሳይጨናነቁ ለፈተና እንዲዘጋጁ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል።