Fana: At a Speed of Life!

የሚዲያ ተቋማትን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የኢትዮጵያ ብሮድካሰት ባለስልጣን የሚዲያ ተቋማትን ከሳይበር ጥቃት መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ የሚዲያ ተቋማትን ከማንኛውም የሳይበር ጥቃት በመከላከል አስተማማኝና ደህንነታቸው የተረጋገጠ የሚዲያ ተቋማት መገንባትን ያለመ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ተናግረዋል፡፡

ባለፈው በጀት አመት ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ዘርፎች፤ ከፋይናንስ ተቋማት በመቀጠል የሚዲያ ዘርፉ በ2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ዶክተር ሹመቴ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን መረጃን በትክክል ለአድማጭ ተመልካች የማድረስ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው ለዚህም መረጃዎቹ ከሳይበር ጥቃት ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ መዘዋወር እንደሚገባቸዉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንጻር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መረጃ ደህንነቱን ጠብቆ በሚመለከተዉ አካል እጅ ብቻ አንዲቆይ የመጠበቅ ሃላፊነት ላይ ያለው አስተዋፅዎ ቁልፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ባህሪን መሰረት ያደረገ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት ዝርጋታ፣ ሚዲያ ክትትል ሂደቱን የማዘመን ፣ የሳይበር ደህንነት ምርመራ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ባለስልጣኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በቀጣይ በጋራ የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸዉን ዶክተር ጌታቸዉ ገልጸዋል፡፡

ስለ ሳይበር ደህንነት ጉዳይ በስፋት አልተነገረም ያሉት ዳይሬክተሩ የቴክኖሎጂን ጥቅም ብዙዎቹ እያወቁ እና እየተጠቀሙ ቢሆንም አንዴ የተገበርናቸዉን ቴክኖሎጂዎች ያለምንም እክል ለረጅም ጊዜ ብንጠቀም ምንም አይፈጠርም የሚል አስተሳሰብ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለመቀየር እና ሊገጥሙ የሚችሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለመሙላት ሚዲያዎች ጥሩ የማስተማሪያ አማራጮች መሆናቸውንም ዶክተር ጌታቸዉ መግለፃቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.