በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ታማኝ ግብር ከፋይ ባለሀብቶች እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ በክልሉ በታማኝነት ግብርና ታክስ ሲከፍሉ ለቆዩ ባለሀብቶች በዛሬው እለት እውቅና ሰጥቷል።
አዳማ በተካሄደው በዚህ ስነስርዓት ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና ምክትላቸው ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ተገኝተዋል።
አቶ ሽመልስ በዚሁ ወቅት አገር ልትገነባ የምትችለውም ዜጎቿ በሐቀኝነት የሚጠበቅባቸውን ግብር ሲከፍሉ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፈው ለአገሪቱ የሚጠበቅባቸውን ገቢ ለከፈሉ ወገኖችም ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።
የክልሉ የገቢዎች ቢሮ ዳይሬክተር ወይዘሮ መስከረም ዳባ በበኩላቸው÷ በክልሉ በታማኝነት ግብር የሚከፍሉ ባለሀብቶች ለሌሎችም ጥሩ ዓርዓያ ናቸው ብለዋል።
በዛሬው የእውቅና አሰጣጥ ስነስርዓት ላይም 126 ባለሀብቶች እውቅና እንደተሰጣቸው ተገልጿል።
በዚህም መሰረት እስከ 1 ሚሊየን ብር የከፈሉ 48 ባለሀብቶች በብር ደረጃ ተሸላሚ ፣ ከ 1እስከ 10 ሚሊየን ብር የከፈሉ 53 ባለሀብቶች የወርቅ ደረጃ ተሸላሚ ሲሆኑ ከ 10 እስከ 53 ሚሊየን የከፈሉ 16 ባለሀብቶች ደግሞ በፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከዚያም ባለፈ ከ53 እስከ 113 ሚሊየን ብር ግብርና ታክስ የከፈሉ 3 ባለሀብቶች ከፍተኛውን የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
በብዙዓለም ቤኛ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።