የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ ተወካይ እና የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንትን ተቀብለው አነጋገሩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ ተወካይ እና የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን ክቡር ጆሴፕ ቦረልን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን እና የአውሮፓ ህብረትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው መምከራቸው ተሰምቷል።
የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የህብረቱ አባል አገራት ለኢትዮጵያ እያደረጉት ስላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አቶ ገዱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በተሻለ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ምንጊዜም እንደምትሰራ አቶ ገዱ በዚህ ወቅት አረጋግጠዋል።
አቶ ገዱ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተካሄደ ስላለው አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለጻ አድርገዋል።
በውይይታቸው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ እያደረጉት ስላለው ውይይት እና ድርድር በተመለከተም መረጃ ተለዋውጠዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስሩ ይበልጥ እንዲጠናከር ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን እንቅስቅሴ በተመለከተም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ቦረል በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ለውጥ ማድነቃቸው ተነግሯል።
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክትል ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወቅት አጋግጠዋል።
ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣይ በዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰብአዊ ልማት፣ በህገ ወጥ የሰዎች ፍልሰት እና መሰል ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚንቀሳቀሰም ምክትል ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንት በአትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ በህብረቱ ድጋፍ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከናወኑ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን እንደሚጎበኙም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።