ከተማ አስተዳደሩ ለአማራ ክልል የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው መታሰቢያ ህንጻ ማሰሪያ የመሬት ካርታ አበረከተ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአማራ ክልል የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን መታሰቢያ ህንጻ ማሰሪያ የመሬት ካርታ አበረከተ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለመታሰቢያ ህንጻ ማሰሪያ የሚሆን ቦታ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ውስጥ 2 ሺህ 250 ካሬ ሜትር የመሬት ካርታለሠማዕቱ ቤተሰቦች አስረክበዋል፡፡
ወይዘሮ አዳነች በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ጀግኖቻችንን ለማሠብ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸው ወደፊትም ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው መቆሙን ይቀጥላል ብለዋል።
አክለውም ሰማዕታት ጓዶቻችን ለሀገር እና ለህዝብ ሲሉ ቀን ከሌት ሲታትሩ የነበሩ በመሆኑ ታሪካቸው ከመቃብር በላይ ነውና ሁልጊዜም ስንዘክራቸው እንኖራለን ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከአሁን ቀደም የዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የአቶ ምግባሩ ከበደ እና የአቶ እዘዝ ዋሴን ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት የሠጠና እንዲሁም ለኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሰዓረ መኮንን 1 ሺህ ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መስጠቱን አስታውሷል፡፡