Fana: At a Speed of Life!

በተባበረ ሃገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሃይቅ ላይ ለማስወገድ የሚያስችል ዘመቻ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተባበረ ሃገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሃይቅ ላይ ለማስወገድ የሚስችል ዘመቻ ሊጀመር መሆኑ ተገለፀ፡፡
ዘመቻውን አስመልክቶ በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውይይት ተካሂዷል።
በዘመቻው እንቦጭን ከጣና ሃይቅ ላይ ለማስወገድ ሁሉንም ክልሎች ከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተዘጋጀ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።
በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ እንደገለጹት እንቦጭ በጣና ሃይቅና በአባይ ተፋሰስ ላይ 3 ሺህ ሄክታር የሚገመት የውሃው አካል ላይ ተንሰራፍቷል፡፡
እንቦጭ የተንሰራፋበትን የውሃ አካል ለማጽዳት ሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት 3 ሺውን ሄክታር በመከፋፈል በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የሚያስወግዱት ይሆናል ነው የተባለው፡፡
አረሙን ከውሃው ላይ ማስወገድ፤ መንቀል ፤በአንድ ቦታ ማከማቸትና ማቃጠል ወይንም መቅበር በዘመቻው የሚሰራበት መፍትሄ መሆኑም ታውቋል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ ለአንድ ወር በሚካሄደው በዚህ ዘመቻ ላይ ሁሉም ክልሎች ፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ተቋማትና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለይም ደግሞ ባለሃብቱ በንቃት እንዲሳተፍበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማት ለዘመቻው ስኬታማነት ከተለመደው አሰራር ባሻገር ማቀድና ስራውን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፋንታሁን ማንደፍሮ በበኩላቸው ይህ እቅድ በአግባቡ የሚተገበር ከሆነ እንቦጭ የሚስከትለውን ጉዳት መቀነስ እንችላለን ነው ያሉት፡፡
በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው ለዚህ ዘመቻ 92 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የተጠቀሰ ሲሆን ለዘመቻው እስከ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለማሳተፍ መታቀዱን ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.