የደቡብ ወሎ ዞን የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየሰፋ ነው
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየሰፋ መምጣቱን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ገለፀ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የዞኑ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ እንደገለፁት መንጋው ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ የተከሰተ ቢሆንም አሁን ላይ ሰፊ አካባቢን በመሸፈን በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።
ዞኑ ውስጥ ካሉ 21 ወረዳዎችም በተለይ በወረባቦ ወረዳ 12 ቀበሌዎች ላይ እና በአርጎባ ወረዳ ደግሞ በአንድ ቀበሌ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።
እስካሁንም የ8 ሺህ197 አርሶ አደሮች ማሳ ጉዳት ደርሶበታል ያሉት አቶ ታደለ ጉዳቱ ሰሞኑን ከአቅም በላይ እንደነበር አንስተው ዛሬ መጠነኛ መቀነስ ማሳየቱን ገልፀዋል።
በዚህ ከቀጠለ የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል የሚያሳይ ነው ብለዋል አቶ ታደሰ።
ጭስ ማጨስ ፣ ድምፅ ማሰማት እና የመሳሰሉት ባህላዊ መንገዶችን በመጠቀም ሰብል ላይ እንዳያርፍ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉ ሲሆን ባለሙያዎችን እና ወጣቶችን በማስተባበር የኬሚካል ርጭትም እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአውሮፕላን ርጭትም በአማራጭነት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ያሉት አቶ ታደሰ፣ በፌደራል ግብርና ቢሮ በኩል ድጋፍ አልተለየንም፣ እያደረሰ ካለው ጉዳት አንፃር ግን ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አክለውም ከስርጭቱ አንፃር ለሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተመደበው አንድ አውሮፕላን በቂ አለመሆኑን ተመልክተናል፣ ተጨማሪ አውሮፕላን ቢኖር ችግሩን መቀነስ ይቻል ነበር ብለዋል።
በቀጣይ ጊዜያትም ጉዳቱ ሊጨምር ስለሚችል ተጨማሪ አውሮፕላን እና በቂ ትኩረት ያስፈልጋል ያሉት የግብርና ቢሮ ሃላፊው ሰብሉ እያደገ በሄደ መጠን ተጋላጭ እንደሚሆን ተናግረው የአርሶ አደሩን ሰብል ለመታደግ በርብርብ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ