አርመኒያ እና አዘርባጃን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ደረሱ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አርመኒያ እና አዘርባጃን በናጎርኖ ካራባህ ግዛት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሁለቱ ሃገራት በሞስኮ ለ10 ሰአታት ከተወያዩ በኋላ የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከስምምነቱ መደረስ በኋላም ሃገራቱ ገንቢ ውይይት ያደርጋሉም ነው ያሉት ላቭሮቭ፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎም ሃገራቱ ከዛሬ ጀምሮ የእስረኞች ልውውጥ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
የአዘርባጃን አካል እንደሆነች የሚነገርለትና የግጭታቸው መንስኤ የሆነው ናጎርኖ ካራባህ ግዛት በአርመኒያውያን ይተዳደራል፡፡
ሁለቱ ሃገራት ከፈረንጆቹ 1988 እስከ 1994 ድረስ በክልሉ ይገባኛል ጉዳይ ጦር ተማዘው ነበር፡፡
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግጭት ውስጥ ባይገቡም በክልሉ የባለቤትነት ጉዳይም ሆነ በሰፈራ ፕሮግራም ላይ ግን ምንም አይነት ስምምነት ደርሰው አያውቁም፡፡
የዛሬ ሁለት ሳምንት ዳግም በጀመረው የሁለቱ ሃገራት ግጭት ሳቢያም እስካሁን ከ300 በላይ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ መፈናቀላቸው ይነገራል፡፡
ምንጭ፦ ቢቢሲ