የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላም ፌስቲቫል ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላም ፌስቲቫል የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በተገኙበት ተካሄዷል፡፡
ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ በሰላም ፌስቲቫሉ ላይ ባደረጉት ንግግር ሰላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ ለፀጥታ ኃይሉ ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል።
ዕድገትና ልማት ሊመጣ የሚችለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ይህንን የተረዳው የክልሉ ህዝብ ጉዳዩን በታላቅ ኃላፊነት እየተወጣው እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት፡፡
ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ የሃይማኖት አባቶች በአስተምህሮታቸው የሀገር ሽማግሌዎች በምክራቸው ስለሰላም ሊሰብኩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
እንዲሁም ወጣቶችም በሰከነ መንገድ ችግሮች እንዲፈቱ ዕድልና ሐሳብ እንዲሰጡ አመላክተዋል።
ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በሚከናወነው እምቦጭን ከጣና ሐይቅ የማስወገድ ሥራ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ጣናን የወረረውን እምቦጭ ለማስወገድ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸው ዘመቻው በሚቀጥለው ሳምንት በይፋ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላም ፌስቲቫል ለዞኑና ለክልሉ ሰላም መጠበቅ አስተዋፅዖ የነበራቸውን 55 የፀጥታ አባላት የማዕረግ ዕድገት በመስጠት መጠናቀቁን አብመድ ዘግቧል።