የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 76 ነጥብ 35 በመቶ ደረሰ – የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 76 ነጥብ 35 በመቶ መድረሱን አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ በመስኖ ልማት፣ በኢነርጂ እንዲሁም በተፋሰስና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ የ2013 የሩብ ዓመት የስራ ዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ በ2013 ዓ.ም ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ ለማስቻል በሩብ ዓመቱ የግንባታውን አፈፃፀም በ1 ነጥብ 6 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ በ2 ነጥብ 5 በመቶ ለማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በዚህም በሩብ ዓመቱ የግንባታውን አፈፃፀም ከታቀደው በላይ ለማከናወን መቻሉን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በመስኖ ግድቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ በመያዙ የተያዘውን ውሃ ወደ ልማት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ስለሺ ገልፀዋል፡፡
በንፁህ መጠጥ ውሃ እና በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ዙሪያም በሩብ ዓመቱ አበረታች ሥራ መሰራቱን ሚንስትሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የአየር ክልል ከበረራ ነፃ እንዲሆን የተደረገው ያለውን የደህንነት ስጋት ለማስቀረት ነው ብለዋል፡፡
በዕቅዱ መሰረት በተያዘው ዓመት የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ እንደሚደረግም ማረጋገጣቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡