በሀረሪ ክልል ከ300 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረሪ ክልል ከ300 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተመረቁ።
በምረቃ ስነስርዓቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሩ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላና ሌሎች የካቢኔ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮችም ተገኝተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በስነስርዓቱ ወቅት ፕሮጀክቶቹ የክልሉን ህብረተሰብ የልማት ጥያቄ ከመመለስ አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከልም ከታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ቀድመው እንደተጠናቀቁ ጠቅሰው በቀጣይም ይህ ተግባር አጠናክሮ ከመቀጠል አንጻር በትኩረት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የመንግስታዊ ተቋማት የቢሮ እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል እና ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር የተገልጋዩን እርካታን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ ምርቱን ለተጠቃሚ ማድረስ የሚያስችለው የመንገድ ፕሮጀክት ስራን በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ መሳካትም የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበረ ጠቁመው በቀጣይም ይህ ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ተግባራዊ የሆኑ ፕሮጀክቶች የክልሉን ህዝብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥና የልማት ጥያቄዎችን የሚመልስ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው በእለቱ ከመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሁም በትምህርት በግብርናና ሌሎች ዘርፎች ላይ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል።
እንዲሁም በከተማው ኤረር በር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ እስከ ገጠሩ ኤረር ወልዲያ ድረስ የሚዘልቀው የ13 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ፕሮጀክትም በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
ይህም የህብረተሰቡ ከመሠረተ ልማት እና ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ሲያነሳው የነበረውን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የክልሉ ህዝቡ ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሰራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በእለቱ የአፈጉባኤ ህንፃ፣የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ ዲጂታል ላይብረሪ፣ አፈ-ጉባኤ መሰብሰቢያ ዘመናዊ አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ዶሮ እርባታ ማዕከል ማስፋፊያ እንዲሁም የመንገድና እና የመብራት ፕሮጀክት በእለቱ የተመረቁ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ከክልሉ ኮሚኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።