የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ ኢትዮጵያ የጤና ዘርፉን በጀት በ46 በመቶ አሳድጋለች- ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ ኢትዮጵያ የጤና ዘርፉን በጀት 46 በመቶ ማሳደጓን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የቁሳቁሶች ፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና የግል ጤና መጠበቂያ መሳሪያዎች ፍላጎት መጨመሩን ፋይናንሺያል ታይምስ ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል።
በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደው ውይይት ላይ በበርካታ አፍሪካ ሀገራት የጤና ዘርፉ የተረሳ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሮና ቫይረስ ደካማ ጎናችንን አሳይቷል ብለዋል።
ለጤና ዘርፉ የዋለው ተጨማሪ ወጪ የጤናው ዘርፍ በሀገሪቱ በበጀት ክፍፍል አራተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታልም ነው ያሉት።
በዘንድሮው የበጀት አመትም ለጤናው ዘርፍ 18 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የተመደበ ሲሆን ይህም ከቀደመው በጀት አመት የ12 ነጥብ 64 ቢሊየን ብር አንጻር ብልጫ ያለው ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ካስከተለው ጉዳት አንፃር ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት በሞት እና በቫይረሱ በመያዝ የደረሰባቸው ጉዳት ከባድ ነው ባይባልም የአካባቢው ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱንም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ሀገራት የአረንጓዴ አሻራን በመከተል እና በታዳሽ ሀይል ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከኢትዮጵያ ልምድ እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፥ ሬውተርስ