Fana: At a Speed of Life!

ዶናልድ ትራምፕ ሱዳንን አሸባሪነትን ከሚደግፉ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ሊሰርዟት ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳንን አሸባሪነትን ከሚደግፉ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ሊሰርዟት ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህ የሚሆነው ግን ሱዳን በፈረንጆቹ1998 በኬንያ እና ታንዛኒያ በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ለተጎዱ እና በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካውያን 335 ሚሊየን ዶላር ካሳ ከከፈለች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሱዳን መንግስት የተጠየቀውን ካሳ በፈቃደኝነት ገቢ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው “መልካም ዜና ነው፤ በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገ ያለው አዲሱ የሱዳን መንግሥት ለሽብር ጥቃቱ ሰለባዎችና ቤተሰቦቻቸው 335 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል” ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ገንዘቡ ገቢ ከተደረገ በኋላ ሱዳንን ከዝርዝሩ አስወጣታለሁም ነው ያሉት፡፡

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በበኩላቸው ትራምፕ የጠየቁት የካሳ ክፍያ ገንዘብ ቢተላለፍም ከአሜሪካ በኩል ምላሸ አለመምጣቱን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳን በዝርዝሩ መካተት ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈላት ጠቅሰው ገንዘቡ መከፈሉ ለሱዳን ከዝርዝሩ መውጣት የመጨረሻ ዋስትና መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በፈረንጆቹ 1998 በሁለቱ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት 220 ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ በርካቶችም ቆስለዋል፡፡

የካሳ ክፍያውም በወቅቱ በተፈጸመው ጥቃት ለህልፈት ለተዳረጉ ተጠቂዎችና ለጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች የሚከፈል ነው ተብሏል፡፡

ሱዳን ከፈረንጆቹ 1993 ጀምሮ በአሜሪካ ሽብርተኝነትን በሚደግፉ ሃገራት ዝርዝር ጥቁር መዝገብ ውስጥ ሰፍራ ትገኛለች፡፡

ለዚህ ደግሞ የቀድሞው የአል ቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን በሃገሪቱ መንግስት ጋባዥነት በእንግድነት በሱዳን ማሳለፉ ምክንያት እንደነበር ይነገራል፡፡

ሱዳን በጥቁር መዝገብ ውስጥ መስፈሯን ተከትሎም ኢኮኖሚዋ ላይ ጫና ፈጥሮባት ቆይቷል፡፡

ሃገሪቱን ለረጅም አመታት የመሩት የቀድሞው መሪ ኦማር ሃሰን አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ግን የሃገራቱ ግንኙነት መሻሻል እየታየበት ነው፡፡

ትራምፕም ቃላቸውን ጠብቀው ሱዳንን ከዝርዝሩ የሚያስወጧት ከሆነ ለሃገሪቱ መንግስትና በርካታ ማነቆዎች ለተደራረቡበት የሱዳን ኢኮኖሚ ትልቅ የምስራች እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፥ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.