በሀገሪቱ ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታና የተቋማት ሚና ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት ፣ 10 ፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በሀገሪቱ ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታና የተቋማት ሚና ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በተዘጋጀው ውይይት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚህም የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት፣ መንግስት የፈፀማቸው የለውጥ ተግባራት እንደ መልካም ጅማሮ የታየ ሲሆን፤ በአንፃሩ የመብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ የመሸፋፈን፣ የፍትህ አካላት ህግ የማስከበር ግዴታን አለመወጣት ደግሞ በድክመት ተነስቷል።
ግጭቶች ሲፈጠሩ ነገሮች ላይ ከማሳበብ ይልቅ ለሰው ህይወት ቅድሚያ በመስጠት ሊሰራ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ከሰብአዊ መብቶች ጋር በተያያዘ ጥናታዊ ፅሁፎች እየቀረቡ ሲሆን በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶች እና መፍትሄያቸው እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ሚናን በተመለከተ ምክክር እንደሚደረግ ኢዜአ ዘግቧል።