በሩብ ዓመቱ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ 40 ሚሊየን ዶላር ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሩብ ዓመቱ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ባለፉት ሶስት ወራት 40 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት ገለጸ።
ኢንስቲቲዩቱ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምና የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ዙሪያ ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም የሩብ ዓመት አፈጻጸም፣ የዘርፉ ነባራዊ ሁኔታ፣ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ መዳሰሱ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ በዓለም ለተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የደህንነት መከላከያ አልባሳት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ እንደነበረም ተናግረዋል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተቀዛቀዙ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ መመለስ፣ ከገዥዎች ጋር ማገናኘት እና የወጪ ንግዱን ማስቀጠል በዕቅዱ መካተታቸውን ገልፀዋል።
ኢንስቲቲዩቱ የሃገሪቱን የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ባገናዘበ መልኩ ዕቅድ ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ዕቅዱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለኢንዱስትሪ የሚሆን ግብዓት በሀገር ውስጥ ማምረትና የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረጉንም ነው የገለጹት።
ለዘርፉ የሚያስፈልጉትን ግብዓት ከማሟላት አንፃር በ2022 ዓ.ም የጥጥ የመሬት ሽፋን ከነበረበት 55 ሄክታር ወደ 411 በማሳደግ 2 ነጥብ 35 ቶን ጥጥ ለማምረት መታቀዱን ገልፀዋል።
የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት፣ የምርት ጥራታቸውን በማስጠበቅና የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት መታቀዱንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በ2022 ዓ.ም ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ወደ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ መታቀዱን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡