የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በህዳሴ ግድብ ላይ የሰጡት አስተያያት ”ኃላፊነት የጎደለው ነው”… የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች
አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሰጡት አስተያያት ”ኃላፊነት የጎደለው ነው” ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች ተናገሩ።
ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡት ተደራዳሪዎቹ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖና አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ፕሬዚዳንቱ ግድቡን አስመልክተው የሰነዘሩት አስተያየት ”ኃላፊነት የጎደለው” ነው ብለውታል።
የግድቡ ተደራዳሪና የአባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥታት እንዲሁም በሁለቱ አገሮች ህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን የረጅም ጊዜ ጠንካራ ትብብር ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ገልጸዋል።
“ግብጽ በኢትዮጵያ ጦርነት እንድታውጅ ድጋፍ የሚያደርግ ንግግር ማድረግ የማይጠበቅ ኃላፊነት የጎደለውና የማይቻል ነው”ብለዋል።
የኢትዮጵያ አጋሮች፣የአሜሪካ የኮንግረስ አባላትና በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ንግግሩን ”በጠንካራ ሁኔታ” እንዲያወግዙት ዶክተር ያዕቆብ ጠይቀዋል።
“የተለያዩ አካላት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች እጃቸውን ሲያስገቡ ይሄን በፍጹም የማንፈቅደውና የማንቀበለው ነው የሚል ሕዝባዊ ተሳትፎና አንድነት ያስፈልጋል። ለዚህም ኢትዮጵያውያንም ለመብቶቻቸው መጠበቅ በጽናት በጋራ መቆም ይገባቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
የቀድሞ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ በበኩላቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በግድቡ ዙሪያ የሰጡት አስተያያት በግላቸው እንደያዙት አቋም ሊታይ እንደሚገባና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የአብዛኛውን የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት አይወክልም ብለዋል።
ኢትዮጵያና አሜሪካ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው አስታውሰው፣ የአንዲት አገር ሉዓላዊነት በመዳፈር ጦርነት ማወጅ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
”ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ዋጋ ከፍለው የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ወደ ኋላ አይሉም። ይሄንንም ታሪክ ይነግረናል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።