ገለልተኛ የአማካሪዎች ቡድንና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ገለልተኛ የአማካሪዎች ቡድንና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ከክልል እስከ ቀበሌ ባሉ አደረጃጀቶች ለፖሊስ አገልግሎት እውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን እና ድጋፋቸውን የሚሰጡ ገለልተኛ የአማካሪዎች ቡድን ማቋቋሙን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አገልግሎት ወንጀል መከላከልና የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል የሚሳተፉ በጎ ፈቃደኛ የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት በቀበሌ እና በወረዳ ደረጃ መቋቋሙን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በክልል ደረጃ የተቋቋመው ገለልተኛ የአማካሪ ቡድን 15 በጎ ፈቃደኛ አባላት ሲኖሩት በክልልሉ ሁሉም ዞኖች አጠቃላይ 234 አባላት ያሉት ገለልተኛ አጣሪ ቡድንም ተቋቁሟል፡፡
ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ በክልሉ ውስጥ 239 በወረዳዎችና በ3 ሺህ 60 ቀበሌዎች የሚደራጅ ሲሆን በቀሪ ሦስት ወረዳዎችና የተወሰኑ ቀበሌዎች በቀጣይ እንደሚደራጅም ተጠቁሟል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ መግለጫ ቡድኑ በ201 ወረዳዎች ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ወደተግባር የገባ ሲሆን በቀሪ 41 ወረዳዎች ደግሞ በቀጣይ ይደራጃል፡፡
በየደረጃው የተቋቋመው ገለልተኛ የአማካሪ ቡድን ተጠሪነቱ በየደረጃው ላሉ የፖሊስ ኃላፊዎች እንደሚሆን መናገራቸውንም አብመድ ዘግቧል፡፡
የአገልግሎት ዘመናቸው ለሦስት ዓመታት ሲሆን የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ቡድኖችም ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ነው ያስታወቁት፡፡