የኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ውህደት ፈጸሙ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በይፋ ውህደት ፈጸሙ፡፡
ሁለቱ የአሰሪ ኮንፌዴሬሽኖች በይፋ የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን በሚል ስያሜ ነው ውህደት የፈጸሙት፡፡
ውህደቱን ለማከናወንም ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውንና ለዚሁ ስኬት መብቃታቸው ተገልጿል፡፡
ውህደቱን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አሰሪዎች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመገንባትና ብሄራዊ ጥቅምን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠበቅ ውህደቱ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የአሰሪዎች ጥቅምና መብት ይበልጥ እንዲጠበቅ ለማድረግ ብሎም ከሰራተኛ ማህበራት ጋር የሁለትዮሽ እንዲሁም መንግስትን ጨምሮ የሶስትዮሽ የምክከር ስርአት ውጤታማ እንዲሆን ውህደቱ ሚና እንዳለው መግለፃቸውን ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡