ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ
የክልሉ ሕዝብና መንግስት ሕወኃት ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን ሴራ ለማክሸፍ በጋራ የሚሠሩበት ወቅት ነው።
ሕወኃት ትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ያደረሰው ጥቃትና በሰሜን ዕዝ ያደረሰው የመዝረፍ ሙከራ ቡድኑ ሀገርን ለማፍረስ ወደኋላ እንደማይል በተግባር ያሳየበት ነው፡፡ በዚህም የክልሉ ሕዝብና መንግስት እጅጉን አዝነናል፤ ደርጊቱንም በጽኑ የምናወግዘው ነው፡፡
ድርጊቱ፣ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ አንግቦ የሕዝብን ሠላምና የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር የማይመጥን ነው።
ሕወኃት በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተለያዩ አኩራፊ እና የሀገርን ሠላም ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር ጋብቻ በመመስረት ሕዝቡ በሠላም እንዳይኖር አበክሮ ሲሠራ መቆየቱ መግለጹ ይታወቃል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮች እና የደረሱ ጉዳቶችም በዚህ መልኩ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሕወኃት የውስጥ ኃይሎችን ለዚህ እኩይ ተግባር በመግፋትና የጥፋት እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በመሆኑም አሁን የክልሉ ሕዝብና መንግስት ሕወኃት የጀመረውን ሀገር የማፍረስ ግልጽ እንቅስቃሴ በጋራ ቆመው የሚታገሉበት ወቅት ነው፡፡ካለፈው የከፋ ችግር እንዳያጋጥም ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የጥፋት ተልዕኮን ለማክሸፍ ከምንጊዜውም በላይ የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብና መንግስትም ሕወኃት የጀመረውን ሀገር የማፍረስ ግልጽ እንቅስቃሴ ለማክሸፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
በክልሉ የምትገኙ ብሔር ብሔር ብሔረሰቦችና በየደረጃው የምትገኙ የክልሉ የጸጥታ አካላት መንግስት የሚያስቀምጣቸውን አቅጣጫዎች በተገቢው መልኩ በመተግበር፣ ለአካባቢያችሁ ሠላምና ደህንነት በተደራጀ መልኩ በንቃት እንድትቆሙና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት
ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም
አሶሳ፣