Fana: At a Speed of Life!

መንግስት እና የጸጥታ አካላት ለሚያደርጉት ህዝባዊ ጥሪ ህበረተሰቡ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)መንግስት እና የጸጥታ አካላት ለሚያደርጉት ህዝባዊ ጥሪ ህበረተሰቡ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡
 
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
 
በመግለጫቸውም ህብረተሰቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመቆም መረጃ በመስጠት እና አጥፊ ኃይሎችን በማጋለጥ እንዲተባበር አሳስበዋል፡፡
 
የፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የሃገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ በከፍተኛ ዝግጅት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
 
ኮሚሽነር ጀነራሉ እንዳስታወቁት በህወኃት ውስጥ ያለ የጥፋት ቡድን ጦርነቱን ለመቀስቀስ በትግራይ ክልል በፌደራል ፖሊስ ላይ እና እየጠበቃቸው በነበሩ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽሞ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
 
በዚህም ተቋማቱ መዘረፋቸውን ተናግረው ለውጊያ ሳይሆን ለጥበቃ ስምሪት በተሰጠው ፌደራል ፖሊስ ላይ በተደራጀ እና ለጦርነት በተዘጋጀ ኃይል የተፈጸመው ጥቃት እጅግ አሳፋሪ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
ፌደራል ፖሊስ የተከፈተበትን ጥቃት ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመሆን መክቶ ማጥቃት መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡
 
ይህ የጥፋት ቡድን በትግራይ ከቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈ በሌሎች የሃገሪቱ ከተሞችም ሰርጎ ገቦችን ለሽብር ማሰማራቱ ተደርሶበት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን በቀጣይነትም የፌደራል፣ የክልል ፖሊሶችና ህዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው ሚሊሻዎች ሁሉንም አካባቢዎች በንቃት እንዲጠብቁ ስምሪት ተሰጥቷል፡፡
 
የመንግስት እና የህዝብ ተቋማትን በአግባቡ መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ ኢንቨስትመንትንና ትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮችን ማስተጓጎል በሃገር ላይ ከተቃጣው ጦርነት በእኩል ይታያልም ብለዋል፡፡
 
የህዝቡን የዕለት ተዕለት ተግባር እንዳይተጓጎል መስራት እንደሚጠበቅም ያስታወቁት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ህብረተሰቡም እንደተለመደው እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተሰማራ ኃይልን አሳልፎ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡
 
ባለፉት ቀናት ህብረተሰቡ ትልቅ ድጋፍ ማድረጉም ገልፀው በሁለት ቀን ውስጥ ከ1 ሺህ 500 በላይ ጥቆማዎችን ህብረተሰቡ ማድሱንም አስታወቀዋል፡፡
 
በአልዓዛር ታደለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.