ግጭቱ ከትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን በህወሓት ውስጥ ባለ ቡድን እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ነው- አቶ ሚኪ ተስፋዬ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴራ ፖለቲካ አራማጁ ህወሓት ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚካሄድ ሳይሆን በህወሓት ውስጥ ባለ ቡድን እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የሚደረግ መሆኑን የፈንቅል እንቅስቃሴ የጋራ አመራር እና የትግራይ ወጣቶች አስተባባሪ ገለፁ።
የፈንቅል እንቅስቃሴ የጋራ አመራር እና የትግራይ ወጣቶች አስተባባሪ አቶ ሚኪ ተስፋዬ ፤ የሴራ ፖለቲካ አራማጁ ህወሓት እድሜውን ለማራዘም የመጨረሻ አማራጭ ያለውን ጥቃት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ሰንዝሯል ብለዋል።
ይህን ተከትሎ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ፈንቅል የሚቀበል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ግጭቱ ግን ከትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን በህወሓት ውስጥ ባለ ቡድን እና በመላው ኢትዮጵያን መካከል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል።
የፈንቅል ንቅናቄ አባላት የህወሓት አቋም በትግራይ ክልል ውስጥ በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ ትግል ህወሓትን ማስወገድ እንደማይቻል፤ ስልጣኑንም ለትግራይ ህዝብ እንደማያስረክብ አምነው፤ ህወሓት ሊወገድ የሚችለው እሱ በታጠቀው ልክና አግባብ እኛም ተደራጅተን በህዝባዊ አመጽ ማስወገድ አለብን የሚል አቋም ይዘው መነሳታቸውን አመልክተዋል ።
ህወሓት ቀደም ሲል ለ27 ዓመት ሲገዛ የነበረበት አቋሙን አለመቀየሩ እና ትግራይ ውስጥ ከገባ በኋላ ይሄንኑ አቋም ይዞ ቀጥሏል።
እስካሁንም ከፌዴራል መንግሥቱ ባፈነገጠ መንገድ መከላከያን ከሁለት ለመክፈል ከሚፈጽመው ሴራ ባለፈ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም እርስ በእርሱ እንዲጨፋጨፍ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል ነው ያሉት አቶ ሚኪ።
አሁን ላይ በመከላከያ ላይ ጥቃት እስከመፈጸምም መድረሱን አስታውቀዋል።
“ከህወሓት የቀደመ ባህሪ አንጻር እኛ ጠብቀነው የነበረው በራሱ በህዝቡ ላይ እንደሚፈጽሙት ነበር፤” ያለው አቶ ሚኪ፤ ይሄን የጠበቁበት ምክንያትም ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ ሴራዎችም ይሄንኑ ስለሚያሳዩ እንደሆነም ገልፀዋል።
በህወሓቶች በኩል መከላከያውን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ብዙ ሴራዎች ሲሰሩ እንደነበረ፤ ማህበረሰቡም ከሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ጦርነት እንዲገባ እና ወጣቱም በዛ ስሜት እንዲቀረጽ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር በመጠቆምም፤ ፈንቅል ይሄን ታሳቢ በማድረግ በማህበራዊ ሚዲያዎች ብዙ ሲያጋልጡ መቆየቱን ተናግሯል።
አቶ ሚኪ ህወሓት ከትናንት በስቲያም በመከላከያ ላይ ጥቃት የፈጸመበት ትልቁ ምስጢር፣ የፌዴራል መንግሥት ጦር እንደማያዘምትበት በመረዳቱ እና በተደጋጋሚ የህወሓትን የጦርነት አጀንዳ እያከሸፈበት ስለመጣ የመጨረሻ ምሽጉ እየተሰበረ ስለሄደ ነው ብለዋል።
ያለው አማራጭ ራሱ የፌዴራል መንግሥትን መተንኮስ ስለሆነ ፤ ለዚህ ትንኮሳ ደግሞ ዒላማ ያደረገው መከላከያ እና የአማራ ክልልን ነበር ነው ያሉት።
የመጨረሻ ካርዱን ተጠቅሞ እድሉን ለመሞከር ይሄንን ጥቃት ፈጸመ ያሉት አቶ ሚኪ በዚህ ረገድ በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል አዋሳኝ ያሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች አጠቃላይ በተለይ የአማራ ክልል መንግሥት፤ የትግራይን ህዝብ እና ህወሓትን ነጥሎ ማየት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
የትግራይ ህዝብን ከልዩ ኃይሉና ከህወሓት መለየት ከተቻለ ድሉ የሁሉም ህዝብ ይሆናል ያሉ ሲሆን አሁን ያለው ግጭት ከትግራይ ህዝብ ጋር አይደለም፤ ግጭቱ አጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ እና በህወሓት ውስጥ ባለ ቡድን መካከል እንደሆነ በመጥቀስ።
የፌዴራል መንግሥት እስከዛሬ ድረስ ትዕግስት አድርጓል ብለን ነው የምናምነው የሚሉት አቶ ሚኪ፤ ትንኮሳውን ተከትሎ እየወሰደ ያለው እርምጃም በተመለከተ አረፍል ከሚል በስተቀር ደጋፊዎች ነን ሲሉ ገልፀዋል። በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ወጣትም ከህወሓት ጋር እየተሰለፈ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከህወሓት የተነጠለ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዚህም ሑመራና አካባቢው ህዝቡም ሆነ ወጣቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴው ላይ መሆኑን፤ ሽሬ አካባቢ ያለው ሚሊሻም ህወሓትን አታስፈልጉንም የሚል አቋም መያዙን ጠቁመዋል፤አሁንም የትግራይ ህዝብና ወጣት ፤ ይሄንኑ የተረጋጋና ብስለት የተሞላበት አካሄድ መከተል እንዳለበት ነው የገለፁት።
የትግራይ ህዝብና ወጣት ደግሞ በዚህ መልኩ ከህወሓት ራሱን ሲነጥል አሁን ላይ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ መስራት ያለበት ነገር አለ፤ ምክንያቱም ህወሓት የዘራው መርዝ እና እሱ ያደራጃቸው ኃይሎች በየክልሉ አሉ ብለዋል አቶ ሚኪ ።
እነዚህ ኃይሎች በፋይናንስ ሲደግፋቸው የነበሩ ናቸው፤ እናም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በየቀበሌውና በየወረዳው ተደራጅቶ በንቃት መከታተልና መቆጣጠር አለበት፤ይሄን ማድረግ የሚችልበት እድልም ሰፊ በመሆኑ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።
የፌዴራል መንግሥትም ሆነ መከላከያ ደግሞ የትግራይ ሚዲያዎችን በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለትግራይ ህዝብ ሙሉ መረጃ ማቀበል አለበት ብለን እናምናለን የሚሉት አቶ ሚኪ ምክንያቱም መረጃ አስፈላጊም ለህዝቡ ትልቅ አቅምና መሳሪያም ስለሚሆን፤ በመከላከያው የሚገኙ ድሎች ጭምር በፌዴራል መንግሥት በኩል ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ መድረስ ይኖርባቸዋል።
በዚህ መልኩ ከተሰራም መልካም ውጤት እንደሚገኝ እናምናለን፤በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ህዝብ የተጨቆነ ህዝብ ስለሆነ ከህወሓት የሚጠጋበት ምንም ምክንያት የለም ይላሉ።
አሁን ህወሓት ተደግፎ ያለው ሙሉ በሙሉ በልዩ ኃይልና በሚሊሻ ነው፤ ይህ ደግሞ ከመከላከያ እንደማይዘል አስታውቋል።
የትግራይ ህዝብና ወጣት እንዲሁም የፈንቅል አባላት አሁንም የሰላሙን አቅጣጫ ይዘን ከመከላከያ ጎን መቆም አለብን፤መከላከያው ይህ ጥቃት የተፈጸመበት ደግሞ በንጹህ ልብ አገር እየጠበቁ ባሉበት ወቅት እንደመሆኑም፤ ወጣቱ እንደ ወጣት፣ ህዝቡም እንደ ህዝብ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው ከመከላከያ ጎን በመሆን መከላከያን ማገዝ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የትግራይ ልዩ ኃይልም የህወሓት የሴራ ፖለቲካ መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል፤ምክንያቱም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። የትግራይ ህዝብም ከኢትዮጵያዊነቱ ተነጥሎ የሚታይ ህዝብ አይደለም ነው ያሉት።
ችግሩን አብሮ ታግሎ አብሮ መሻገር ይገባል፤ ህወሓት አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም በዚህ መልኩ የሚደረግ ትግል ከሁለት ቀን የሚያልፍ አይሆንም፤ለመከላከያ ሰራዊት ሞራል መስጠት አለብን ሲሉም አቶ ሚኪ መልዕክት አስተላልፈዋል።