Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በተለያዩ ዞኖች ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሰባት ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር እታገኘሁ ዜና ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ባለፉት ሁለት ቀናት በደቡብ ኦሞ፣ ካፋ፣ ኮንሶና ሸካ ዞኖች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 25 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 4 ሽጉጦችና 11 ተተኳሽ ጥይቶች ተይዘዋል።

እነዚህን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል በደቡብ ኦሞ ጂንካ ከተማ ሁለት ግለሰቦች የአዕምሮ ህመምተኛ መስለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ በህብረተሰቡ ጥቆማ ተይዘው ምርመራ ሲደረግባቸው ስድስት ሞባይል ስልክና 11 የተለያየ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች እንደተገኘባቸውም ተናግረዋል፡፡

ህወሓትና ሀገር ለማፍረስ የሚሯሯጡ ቡድኖች በተለያዩ አካባቢዎች የህዝብን ሠላም ለማደፍረስ የሚያደርጉትን ጥረት ለማክሸፍ የክልሉ የጸጥታ ሀይልና ህብረተሰቡ በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ ነውም ብለዋል።

ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት እንዲከታተልና የሚያጠራጥር ጉዳይ ሲገጥመው በአካባቢው ለሚገኝ የጸጥታ ሀይል እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.