ብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃ ኪነ ሙያ ያለሰጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘው ብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃ ኪነሙያ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የአቅም ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ነብዩ ዳኜ ተመራቂ ሰልጣኞች በሚሰማሩበት መስክ ሃገርንና ህዝብን በማስቀደም በጥብቅ ሙያዊ ስነምግባር የሚሰጣቸውን ስምሪት በብቃት እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ የመረጃ ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ፤ የብሄር ተዋጽኦን ለማስጠበቅና ሃገሪቱን የሚመስል ተቋም ለመገንባት የያዘውን እቅድ እውን ለማድረግም ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሙያዊ የመረጃ ተቋም ለመገንባት በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራሉ ተመራቂዎች በተቋም ግንባታ ሂደቱ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ መጠየቃቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መግለጫ ያመላክታል፡፡
የብሔራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው፥ የመረጃ ኪነ ሙያ ተመራቂዎች ሃገሪቱ የምትገኝበትን ፈታኝና ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ አካሄድ ለቀጣይ ስምሪት የሚያግዛቸውን ትምህርትና ሥልጠና መቅሰማቸውን አመልክተዋል፡፡
የተደራጀ ወንጀልንና ሽብርተኝነትን በመከላከል የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅም ለመጠበቅ የሚስያችላቸውን የንድፈ ሃሳብ እውቀት መቅሰማቸውንና እና ተግባራዊ ልምምድ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡