Fana: At a Speed of Life!

በህወሓት ውስጥ ያለውን ፅንፈኛ ቡድን የሚያወግዝ ሰልፍ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሶማሌ ክልል በህወሓት ውስጥ ያለውን ፅንፈኛ ቡድን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ።
ሰልፉ የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዝ ሲሆን በጅግጅጋ ከተማ ነው የተካሄደው።
በሰላማዊ ሰልፉ ከሶማሌ ክልል ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ሰልፈኞቹ ከሃዲው የህወሓት ጁንታ ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት መፈክሮችን በመያዝ አውግዘዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በወቅቱም ባደረጉት ንግግር÷ ስግብግቡ ጁንታ አፀያፊ ተግባር በሶማሌ ሕዝብ እና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያሳረፈው ቁስል ሳይሽር በቅርቡ የሀገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ተግባርም እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
የሰልፉ ዓላማም ወንበዴው የሕወሓት ቡድን በሥልጣን ዘመኑ ያደረሰውን ግፍ እንዲሁም ከሰሞኑ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት እና አሁንም እያደረገ ያለውን የክህደት ተግባር ለማውገዝ መሆኑን አቶ ሙሰጠፌ አስታውቀዋል።
ተጠያቂነት የማይሰማው ይህ ወንበዴ ቡድን በዘር፣ በሃይማኖት እና በብሔር እያደረገ ያለውን የመከፋፈል ሥራም እንደሚያወግዙት ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የተናገሩት።
ስግብግቡ የሕወሓት ቡድን ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ከባድ በደል አድርሷል ያሉት የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች ÷ በቅርቡ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን አስነዋሪ ጥቃት አውግዘዋል።
ይህ ቡድን የፈፀመው ተግባር አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ ድርጊቱ ችግሮችን በሰላም እና በውይይት ይፈታል የሚለውን ተስፋቸውን ያሟጠጠ እንደሆነም ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹ አክለውም የመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለውን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚደግፉ ገልጸው÷ የእናት ጡት ነካሽ የሆኑትን የቡድኑን አባላት ለሕግ የማቅረብ ሥራም ያለምንም ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጠል ጠይቀዋል።
ሰልፈኞቹ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነትም መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.