ፖሊስ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰራተኞችን በብሄር ለይቶ መዝግቧል በሚል የተሰራጨው ዜና ከእውነት የራቀ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ፖሊስ የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ሰራተኞችን በብሄር ለይቶ መዝግቧል በሚል የተሰራጨው ዜና ከእውነት የራቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይሉ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ፣ ነገር ግን የሕወኃት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች የሆኑ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ተአማኒ እና ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሠረት፣ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል፣ የምርመራ እና የሕግ ማስከበር ሥራውን መቀጠሉንም ነው የገለጸው።
የአማራ ክልል ፖሊስ እና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት የእነዚህን ተጠርጣሪዎች ዝርዝር ከድርጅቱ መዝገብ አመሳክረዋል እንጂ እንደ ተባለው ሠራተኞችን በብሔር ፈርጀው ያለመመዝገባቸውንም ጠቅሷል።
ከአማራ ክልላዊ ብሔራዊ መንግሥት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ፖሊስ የተጥረጣሪዎችን ዝርዝር በማቅረብ በክልሉ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቢሮ መሥራታቸው እንዲረጋገጥለት ጠይቋል እንጂ፣ የሠራተኞች ዝርዝር በብሔር ተለይቶ እንዲቀርብለት አልጠየቀም ነው የተባለው።
መንግሥት የሕግ ማስከበር ሂደቱን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በሚከውንበት በዚህ ወቅት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን የሚክፋፍል እና መሠረተ ቢስ የሆነ መረጃን ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይሉ አሳስቧል