Fana: At a Speed of Life!

አብዬ የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሻለቃ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሱዳን አብዬ የተሰማራው የ23ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ አመራሮችና አባላት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄዱ።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በሱዳን አብዬ ሰሜን ቀጠና ላይዘን ኦፊሰር ብርጋዴር ጀኔራል ዋኘው አለሜ፥ በሰሜን ዕዝ የሰራዊት አባላት ላይ የተፈፀመው ጥቃት እጅግ አሳዛኝና ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው ኃይል ተረጋግቶ ግዳጁ ላይ ትኩረት በማድረግ አንድነቱን በሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

የሻለቃው ዋና አዛዥ ኮለኔል ሐሰን አብደላ በበኩላቸው፥ መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ስራና ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ እየወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ ተገቢና የሚደገፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይ ውስጣዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የግንባታ አቅጣጫዎችን በመከተልና ተልዕኮ ላይ በማተኮር ቀሪ የግዳጅ ጊዜያቶችን ህዝቡንና ሃገሪቱን በሚያኮራ አኳኋን መፈፀም ይገባል ሲሉም ነው የተናገሩት።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ጥቃቱን አውግዘው “በጥቃቱ ሳንረበሽና ሳንደናገጥ ይበልጥ አንድነታችንንና ጓዳዊ ዝምድናችንን አጠናክረን የተሰጠንን ስራና ኃላፊነት በሚገባ በመወጣት የሰላም አምባሳደርነታችንን ማረጋገጥ አለብን” ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.