ኪም ጆንግ ኡን ሰሜን ኮሪያ “ማጥቃትን መሰረት ያደረገ የደህንነት ፖሊሲ” እንደሚያስፈልጋት ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆን ኡን ሃገራቸው “ማጥቃትን መሰረት ያደረገ የደህንነት ፖሊሲ” እንደሚያስፈልጋት ተናገሩ።
ኪም በፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፒዮንግያንግ “አዎንታዊ እና ማጥቃትን መሰረት ያደረገ የደህንነት ፖሊሲ ያስፈልጋታል ማለታቸውን የሃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።
በንግግራቸው ያነሱት “አወንታዊና ማጥቃትን መሰረት ያደረገ የደህንነት ፖሊሲ” አሻሚና ግልጽነት የጎደለው ነው ተብሏል።
ይህ ንግግራቸው ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሳሪያ ምርቷን ለማቆም ከአሜሪካ ጋር እያደረገች ያለውን ድርድር ልታቋርጥ ትችላለች የሚለውን ግምት አጠናክሯል።
አስተያየት ሰጭዎችም ፒዮንግያንግ የኒውክሌር መሳሪያዎችን ዳግም ወደ መሞከር ልትገባ ትችላለች የሚል ሃሳብ እየሰነዘሩ ነው።
ዋሽንግተን በተያዘው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ በኒውክሌር ድርድሩ ዙሪያ የተሻለ ነገር ማቅረብ ካልቻለች ፒዮንግያንግ አዲስ መንገድ እንደምትከተል ዝታለች።
ይህ የኪም ጆንግ ኡንን ንግግርም አሜሪካ እጅግ አሳዛኝ ብላዋለች።
ኪም እና ዶናልድ ትራምፕ በሰኔ ወር በሲንጋፖር እና የካቲት ውስጥ በቬትናም ፊት ለፊት መወያየታቸው ይታወሳል።
እንዲሁም ሁለቱ መሪዎች ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ በምትጋራው አዋሳኝ ቦታ ስብሰባቸውን ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ ይነገራል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ