በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የልዑካን ቡድን በሩዋንዳ ጉብኝት አደረገ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሩዋንዳ ጉብኝት አድርጓል።
የልዑካን ቡድኑ በሃገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ለሩዋንዳው የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ክቡር ለዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ ገለጻ አድርጓል።
አቶ ደመቀ ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል በኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ለውጥ ባስገኛቸው ሁለገብ ጠቀሜታዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በተለይም የህውሓት ጁንታ ቡድን ይህን ለውጥ ተጻሮ መቆሙን፣ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች አክራሪ ቡድኖችን ሲያደራጅ፣ በገንዘብ ሲደግፍና ሲያሰማራ መቆየቱን፤ የሃገሪቱን ህገ መንግስት በመጻረር ህገ ወጥ ምርጫ ማካሄዱንና ይህም በሃገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወገዙን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ይህ ቡድን የፌደራል መንግስትን ህጋዊነት መጻረሩን፣ በቅርቡ ደግሞ በሰሜን የሃገሪቱ ክፍል ከሃያ አመታት በላይ በቆየው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አንስተዋል።
የህወሓት ጁንታ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰላማዊ ህዝባችን ላይ ጥቃት ፈጽሞ የንጹሃንን ህይወት ማጥፋቱን፣ በዚህም ከብዙ ጊዜ ትእግስት በኋላ የፌደራል መንግስት የህግ ማስከበር ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።
የዚህ ዘመቻ ዋና ዋና አላማዎች የህግ የበላይነትን ማስከበር አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብና የአካባቢውን ህዝብ ነጻ ማውጣት መሆኑን፥ ለዚህም ወዳጁ የሆነው የሩዋንዳ ህዝብ ጉዳዩን በደንብ እንዲረዳው መልእክት አስተላልፈዋል።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ በበኩላቸው ሩዋንዳ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሃገር መሆኗን እና የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት አጥብቃ እንደምትመኝም ገልጸዋል።
ሁልጊዜም ከኢትዮጵያ ጋር በጽናት እንደምትቆም ስራው በአጭር ጊዜ የሰብአዊ መብትን ባከበረ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት እና በማንኛውም ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚቆሙ ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ አረጋግጠዋል።
በዚህ ውይይት ላይ የሩዋንዳው የደህንነት ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል ጆሴፍ ዛባይታ ተገኝተው ይህንኑ በሚኒስትሩ የተሰጠውን አስተያየት ደግፈዋል።
አቶ ደመቀ የሚመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ትናንት በኡጋንዳ እና በኬንያ ተመሳሳይ ውይይት ማድረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።