በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸረ ሰላም ሃይሎችን አጀንዳ ተቀብለው ወደ ጫካ የገቡ ወጣቶች ፍላጎቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጹ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጸረ ሰላም ሃይሎችን አጀንዳ ተቀብለው ወደ ጫካ የገቡ ወጣቶች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ፍላጎታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት እንዲያቀርቡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በቀጠናው ላለው የሰላም ዕጦት መፍትሔ ለማበጀት ከማንዱራ ወረዳ ከጉሙዝ ብሄረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር መክረዋል።
በቀጠናው በተወሰኑ ቡድኖች በተፈጠረው አለመረጋጋት በርካታ የብሄረሰቡ እናቶች፣ ህጻናት እንዲሁም ሴቶች በከፍተኛ የማህበራዊ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ተብሏል።
ሀገሪቱን በመበታተን ሰላም እንዳይኖር እየተንቀሳቀሰ ያለውን ”የጁንታውን” አጀንዳ ተቀብለው ለጥፋት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ካልቻሉ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም የልማት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን እየተቻለ አግባብነት በሌለው አጀንዳ ወጣቱ ሰለባ መሆን እንደሌለበት በመግለጽ አሁንም ከድርጊታቸው ተቆጥበው ወደ ሰላም እንዲመጡ የሀገር ሽማግሌዎች ከመቸውም በላይ አስተዋጽዖ ማበርከት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይስሃቅ ዓብዱልቃድር በበኩላቸው በዞኑ ውስጥ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብት ተጠብቆ ባለበት ሰዓት በጠላት በኩል የሚነዛውን አጀንዳ በመቀበል የዜጎችን ህይወት መቅጠፍና ማፈናቀል ዋጋ እንደሚያስከፍል በመረዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በቀጠናው ለረጅም ጊዜ እየተስተዋለ ያለውን የሰላም ዕጦት በአሁኑ ሰዓት መልኩን እየቀየረ ወደ የእርስ በእርስ ግጭት እየተቀየረ በመሆኑ መፍትሄ ለማበጀት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ሁሉም የብሄረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎች ለእኩይ ዓላማ ተልዕኮ አስፈጻሚ የሆነውን ወጣት ለመመለስ እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በወረዳው ህዝብን መታደግ በማይችልና ተራማጅ ባልሆነ መልኩ ለጥፋት ተልዕኮ ወደ ጫካ የገቡ ወጣቶችን በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመለሱ ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል።