የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት ባለው ረጅም ሰልፍ ምክንያት እየተጉላላን ነው- ቅሬታ አቅራቢዎች
አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት ባለው ረጅም ሰልፍ ምክንያት መጉላላታቸውን ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ።
ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅሬታቸውን ያቀረቡት ተገልጋዮች በተለይም በዚህ ሳምንት የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ካርድ ለመሙላት ረጃጅም ሰልፎችን ለመሰለፍ መገደዳቸውን ነው የገለፁት።
ቅሬታቸውን መነሻ በማድረግም የፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት ጋዜጠኞች በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ምልከታ አደርገዋል።
ምልከታውም በካዛንቺስ፣ በዊንጌት፣ በአዲሱ ገበያ፣ በሀብተጊዮርጊስ ድልድይ፣ በጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ እና በሌሎችም ስፍራዎች የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የተደረገ ነው፡፡
በእነዚህ ማዕከላትም በርካታ የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ካርድ ለማስሞላት ረጅም ሰልፎች መሰለፋቸውን መታዘብ ችሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዶክተር ገበየው ሊካሳ ስራ አስፈጻሚ፥ በፊት የነበረው አሰራር ሙሉ በሙሉ ወደ አዲሱ አሰራር ለመቀየር ሲባል የካርድ መሙላትም ሆነ ሌሎች የቅድመ ክፍያ የተመለከቱ አገልግሎቶች ለሁለት ቀናት መቆማቸውን ተከትሎ ይህ መከሰቱን አስታውቀዋል።
በሁለት ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው የሶፍትዌር ቅየራም ባሳለፍነው ማክሰኞ በመላው ሀገሪቱ ባጋጠመው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት ወደ ረቡዕ መሸጋገሩንም አስታውሰዋል።
በዚህም ምክንያት የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዕከላት ላይ ረጅም ሰልፍ መከሰቱን በመጥቀስ አሁን ላይ ግን በተለይም ከትናንት ጀምሮ ሰልፎቹ እየተቃለሉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ 36 ማዕከላት መኖራቸውን ያነሱት ስራ አስፈፃሚው፥ ተገልጋዮችም የግድ ካዛንቺስ እና ሌሎችም ውስን ቦታዎች ብቻ መሄድ ሳይጠበቅባቸው በሁሉም ማዕከላት መገልገል ይችላሉም ብለዋል።
አዲሱ ሶፍትዌር የተቀላጠፈ አግልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስም በቀጣይ ደንበኞች ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መሄድ ሳይጠበቅባቸው እንደ ፖስ ባሉ አገልግሎቶች ካርድ መሙላት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።
በትእግስት አብረሃም