ሜጀር ጀኔራል ገብረመድህን ፍቃዴን ጨምሮ 7 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ፍርድ ቤቱ 12 ተጨማሪ ቀናትን ፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በሃገር ክህደት እና ህገመንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በማሰብ ወንጀል የተጠረጠሩት እነ ሜጀር ጀኔራል ገብረመድህን ፍቃዴን (ወዲ ነጮ) ጨምሮ 7 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ፍርድ ቤቱ 12 ተጨማሪ ቀናትን ለፖሊስ ፈቀደ።
ችሎቱ ለዛሬ በይደር የያዘውን ቀጠሮ ተከትሎ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድቤት ቀርበዋል።
የ5ኛ ተጠርጣሪ በሌላ ህክምና ተቋም ልታከም ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄን ፍርድ ቤቱ መርምሮ በፖሊስ ሆስፒታል መታከማቸወን ጠቁሞ ሪፈር ባልተጻፈበት ሁኔታ ወደ ሌላ ቦታ ልታከም ያሉት ጥያቄ አግባብነት የለውም ሲል ወድቅ አድርጎታል።
የ1ኛ ተጠርጣሪ ያቀረቡተን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለማስተርስ ፕሮግራም ለመማር ፎርም እንድሞላ ይፈቀድልኝ ጥያቄን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ባለበት ሆነው ፎርሙን እንዲሞሉ እንዲመቻች ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የሂሳብ እግድ ይነሳልኝ ጥያቄያቸውን በተመለከተም ችሎቱ እግዱ በፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በሚመለከተው አካል በፌዴራል ከፍተኛ ፈርድቤት 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት መታገዱን ገልጾ መዝገቡን በዚያ መከታተል እንደሚችሉ አስታውቋል።
በሌላ በኩል በህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን ተልዕኮ ተቀብሎ በአሌልቱ ማረሚያ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ላይ ቦምብ ለማፈንዳት ሲሞክር በቁጥጥር ስር ውሏል የተባለው የፌደራል ፖሊስ አባል ለ2ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ተጠርጣሪው ኮንስታብል ረዳኢ ተክሊት ይባላል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሸን መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ከ14 ቀን በፊት በአሌልቱ ማረሚያ ፖሊስ ማሰልጠኛ ቦምብ ሊያፈነዳ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጾ ለተጨማሪ ምርመራ በተሰጠው ጊዜ የሰራውን ስራ ለችሎቱ ገልጿል።
በዚህ ምርመራ ተጠርጣሪው ከህወሓት ተልዕኮ ስለመቀበሉ መረጃ አግኝቻለሁ ብሏል የሁለት ሰው ምስክር መቀበሉን ጠቅሶ በአዲስ አባባ ከተማም ከግብረ አበሮቹ ጋር ቦምብ ለማፈንዳት ሲንቀሳቀስ እንደነበር በሰው ምስክር አረጋግጫለው ሲልም አብራርቷል።
ከሰራው በርካታ ምርመራ ስራ በተጨማሪ ቀረኝ ላላቸው ከተጠርጣሪው ጋር አዲስ አባባ ቦምብ ለማፈንዳት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግብረአበሮችን ለመያዝ፤በእጁ የተገኙ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያን የምርመራ ወጤት ለማምጣት፤ ተጨማሪ የሰው ምስክር ለመቀበል እና ለሌሎች ምርመራ ስራዎች 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ተጨማሪ ቀናት ለምርመራ ጠይቋል።
ተጠርጣሪውም ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል ተከራክሯል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ 13 ቀን ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!