Fana: At a Speed of Life!

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጨኖ ሚሌ ችግኝ ጣቢያን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጨኖ ሚሌ ችግኝ ጣቢያን ጎብኝተዋል፡፡

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጨኖ ሚሌ ችግኝ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ጎሳዬ ጎሮፌ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለተመራው ልዑክ የማዕከሉን የስራ እንቅስቃሴ ባስጎበኙበት ወቅት የተሻሻሉ የማንጎ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ የማከፋፈል ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በአመት እስከ 50 ሺህ ችግኞችን ማልማት የሚያስችል አቅም ያለው ሲሆን ያረጁ የማንጎ ዝርያዎችን በማዳቀል ለአርሶ አደሩ እያከፋፈለ ይገኛል፡፡

ከፍራፍሬ ዝርያዎች ባለፈም ሀገር በቀል የደን ችግኞችን በማፍላት እና ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል በተራቆቱ ቦታዎች ላይ እንዲተከል መደረጉን አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ የአካባቢው አርሶ አደር እንደ ማንጎ እና ሙዝ ያሉ ቋሚ ፍራፍሬዎችን ከማልማት ስራ በተጓዳኝ በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎችን ማልማት ላይ ሊያተኩር ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ እየተከሰተ ያለውን የማንጎ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የግብርና ምርምር ባለሙያዎችን ያካተተ ግብረ ሀይል ወደ ቦታው የሚሰማራ ሲሆን፤ ቡድኑ ከሚያገኘው ግብአት መነሻነትም የችግሩን መንስኤ በማጥናት እልባት ለመስጠት ይሰራል ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች መገኘታቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.