Fana: At a Speed of Life!

በዩኔስኮ የተመዘገበው የማጃንግ የተፈጥሮ ደን በአካባቢው ማህበረሰብ ይበልጥ እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል – የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በዩኔስኮ የተመዘገበው የማጃንግ የተፈጥሮ ደን በአካባቢው ማህበረሰብ ይበልጥ እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

የተፈጥሮ ደኑ በዩኔስኮ የተመዘገበበት 3ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በሜጢ ከተማ ተከብሯል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ቴንኩዌይ ጆክ የደን ሀብቱ በዓለም እውቅና አግኝቶ ከተመዘገበ ሶስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ጠቅሰው፤ ይህም በሀገሪቱ ለተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ቀጣይነት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ላይ በኢንዱስትሪ ልማት በገፉ ሀገራት በሚለቀቅ ካርበን እየደረሰ ያለውን የአየር መዛባት፣ የድርቅ፣ የበረሃማነት መስፋፋት፣ የደን መራቆትና ሌሎች ችግሮችን ለመቋቋም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም የዞኑ ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የደን ሀብቱን ይበልጥ በመጠበቅ ልማቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል ያለሰለሰ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡

የማጃንግ ብሄረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮናስ አበበ በበኩላቸው የማጃንግ ደን ባለ ጣዕም የጫካ ቡና፣ የዱርና የጫካ ማር፣ ኮረሪማ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ እንሰትና ሌሎች የግብርና ውጤቶች የሚመረትበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የማጃንግ ጥብቅ ደን የቆዳ ስፋቱ 225 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ሲሆን በውስጡ 550 የሚደርሱ የእጽዋት፣ ከ180 በላይ የአዕዋፍ፣ 33 የአጥቢ እንስሳትና 20 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች እንደሚገኙበት ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.