የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ73 መምህራን፣ ተማሪዎችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 25፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን አስተጓጉለዋል ባላቸው 73 ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እንደገለጹት፥ ከትምህርትና ከስራ ሙሉ በመሉ እስከማገድ የደረሰው እርምጃ የተወሰደው የመማር ማስተማር ስራውን ሆን ብለው እንዲስተጓጎል ማድረጋቸው በመረጋገጡ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ 11 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከዩኒቨርሲቲው እንዲባረሩ የተደረገ ሲሆን፥ 39 ተማሪዎች ለሁለት አመት፣ ሁለት ተማሪዎች ደግሞ ለአንድ አመት ከትምህርታቸው ታግደዋል።
እንዲሁም ብቁ ዜጋን የመገንባት ሃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው በዩኒቨርሲቲው ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ሁከትና ግጭት በማነሳሳት ሚና የነበራቸው 13 መምህራንም አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።
በአግባቡ ካለማስተማር ጀምሮ ተማሪዎችን ለግጭት በማነሳሳት የተለዩ ሶስት መምህራን ሙሉ በሙሉ ከስራ ሲታገዱ፥ ሶስት መምህራን ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ሌሎች ሰባት መምህራን በቀላል የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲቀጡ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም ከተሰጣቸው ስራና ተግባር ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው ሰባት የአስተዳደር ሰራተኞችና አንድ የጤና ባለሙያም ከስራ እንዲሰናበቱ መወሰኑን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
ሴኔቱ በየደረጃው ባሉ አካላት የቀረቡለትን መረጃዎች በመገምገምና በማጣራት የዩኒቨርሲቲውን የስነ ምግባር ደንብና የአስተዳዳር መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ እርምጃ ወስዷልም ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው ሰላምን ለማስፈን ከመምህራንና ተማሪዎች፣ ከህብረተሰብ ተወካዮችና ከከተማው አመራሮች ጋር በመቀናጀት ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ማድረጉን ጠቅሰው በቅርቡ ከፌደራል መንግስት የመጣው የልዑካን ቡድንም በየደረጃው በተዘጋጁ መድረኮች ተወያይቶ የራሱን ግምገማ ማካሔዱን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲው ተፈጥሮ በነበረ ግጭት በአንድ ተማሪ ህይወት ማለፍና በሌሎችም መቁሰል እንዲሁም በንብረት ጉዳት የተጠረጠሩ ተማሪዎችና የአስተዳዳር ሰራተኞችም በፖሊስ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛውና በኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ተቀብሎ የሚያስተምረው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታታል ላይ እንደሚገኙ የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።